(ዜና ፓርላማ) ግንቦት 6 ቀን ፣ 2017 ዓ.ም፤ የመንግስት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን በዋና ኦዲተር የቀረበበትን የ2015 በጀት አመት የኦዲት ግኝት ለማረም ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ መውሰዱን ማረጋገጡን አመላክቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከዋና ኦዲተር መ/ቤት ከመጡ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በባለስልጣኑ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ ሪፖርት ላይ ተወያይቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ባለስልጣኑ በ2014 እና 2015 በጀት አመት ከነበረበት አሉታዊ የኦዲት አስተያየት (adverse opinion) በሰራቸው ትልልቅ የማስተካከያ ስራዎች ወደ ከጥቂት አስተያየቶች በስተቀር (except for) መምጣቱ በጥንካሬ የሚወሰድና ለሌሎች መስሪያ ቤቶችም በማሳያነት ሊወሰድ እንደሚችል አመላክቷል፡፡

ባለስልጣኑ በተሰብሳቢ እና ተከፋይ ሂሳብ፣ በግዥ፣ በንብረት አያያዝና አስተዳደር በዋና ኦዲተር የቀረበበትን የኦዲት ግኝት  የግዥ ስርአቱን በማዘመን፣ ተሰብሳቢ ገንዘብ በማስመለስና በመሰብሰብ፣ የንብረት አያያዙን በማሻሻል የቀረበበትን ማረም መቻሉን በጥንካሬ አንስቷል።

በሌላ በኩል የገንዘብ ቼኩን ከንብረት ክፍል አውጥቶ በካዝና ብቻ ጠብቆ ማቆየት በቂ ባለመሆኑ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የሚወገድበትን መንገድ መፈለግ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

በቀጣይም ባለስልጣኑ የውስጥ ኦዲተርን ማጠናከር እና በድጋሚ የኦዲት ግኝትእንዳይኖር መጣር እንዳለበትም ነው ቋሚ ኮሚቴው ያስገነዘበው።

የመንግስት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን በዋና ኦዲተር የቀረበበትን የ2015 በጀት አመት የኦዲት ግኝቱን ለማረም ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ መውሰዱ የሚያበረታታ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሀገር የምታድገው ጠንካራ ተቋም፣ ህጋዊ አሰራርና ቅንነት ሲኖር ነው ያሉት ሰብሳቢዋ የተቋሙ ኃላፊዎችም የተሰጣቸውን የኦዲት ግኝት በቅንነት በመቀበልና ግኝቱን እንደመስፈንጠሪያ በመጠቀም ለማሻሻል የሄዱበት ርቀት በጥንካሬ የሚወሰድ ነው ብለዋል።

ትንንሽ የሚመስሉ የሀገር ገንዘብ ሲሰባሰቡ ያላቸው ትርጉም ቀላል ባለመሆኑ በሞትና እና ከሀገር በመልቀቅ መሰብሰብ ያልተቻለው ብር 15.000 መሰብሰብ እንደሚገባ፣ የማይቻል ከሆነ በየአመቱ የሚንከባለል የኦዲት ሪፖርት እንዳይሆን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲያገኝ አሳስበዋል።

አያይዘውም የኦዲት ግኝት ትምህርት የሚወሰድበት በመሆኑ በቀጣይ ተቋሙ የተሻለ ስራ ሰርቶ ምንም ነቀፌታ የሌለበት የኦዲት አስተያየት (clean opinion) ማግኘት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ትዕግስት ረታ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከኦዲት ሪፖርት በኋላ መሰብሰብ ካልተቻለው ብር 15.000 እና ከትንንሽ አስተያየቶች በስተቀር የነበረበትን የኦዲት ግኝት ማረም መቻሉን ለቋሚ ኮሚቴው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ (ኢንጂነር) እና ሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው በዋና ኦዲተር የቀረበው የኦዲት ግኝትና ያንን ተከትሎ ቋሚ ኮሚቴው ያደረገልን ክትትልና ድጋፍ መስሪያ ቤታችን የኦዲት ግኝቱን ከማሻሻል ባሻገር የተሻለ እንዲሆን  ከፍተኛ እገዛ አድርጎልናል ብለዋል።

ለዚህም ባለስልጣኑ ባከናወናቸው ስራዎች ከሰሞኑ የISO ሰርተፊኬት እንደሚያገኝ በማሳያነት አንስተው በቀጣይም ተቋሙ የተሻለ ስራ እንደሚሰራም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

(በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *