
መጋቢት 5፣ 2017ዓ.ም የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን በገቢ እና ወጭ ንግድ እንቅስቃሴ ተጽዕኖ በማድረግ የአገሪቱን የሎጅሰቲከስ አሰራር ያሳድጋሉ ለተባሉ እና ባለስልጣን መስሪያቤቱ ያዘጋጀውን የመገምገሚያ መስፈርት ላሟሉ 3 ተጨማሪ የመልቲሞዳል ኦፕሬተሮች የስራ ፈቃድ ሰጥቷል፣በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት የትራንስፓርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ( ዶ/ር) እንደገለፁት ተጨማሪ የመልቲ ሞዳል አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ወደ ዘርፉ መግባታቸው የሎጅስቲክሱን ዘርፍ ይበልጥ እንደሚያሳልጥ እና በፉክክርና በትብብር በመስራት ለአገራችን የወጭ እና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ እድገት ማምጣት እንደሚያስችል በመጥቀስ ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እና ሚኒስቴር መስሪያቤታቸው አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር)በበኩላቸው የመልቲ ሞዳል አገልግሎት ወጭን እንደሚቀንስ፣ የገቢ ዕቃዎች ደህነነታቸው ተጠብቆ እና ባጠረ ጊዜ ወደ ተፈለጉበት ቦታ ለማድረስ እንደሚረዳ ገልፀው፤ባለሥልጣኑ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ ሶስት የመልቲ ሞዳል ትራንስፓርት አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ወደ ዘርፉ መግባታቸውን አብስረዋል።

በዛሬው መርኃ-ግብር በመልቲሞዳል ትራንስፖርት ኦፕሬተርነት የንግድ ስራ ፈቃድ ያገኙት ኩባንያዎች ኢትዮ ሬል ሎጅስቲክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፣ኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር እና ገልፍ ኢንጎት ኤፍ ዜድ ሲ ኢንደስትሪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆኑ በስራ ላይ ያለው መንግስታዊ የመልሞዳል ትራንስፖርት ኦፕሬተር ጨምሮ አጠቃላይ 7 ኦፕሬተሮች የመልቲሞዳል ትራንስፖርት ዘርፉን ተቀላቅለዋል፡፡
Source: Ethiopian Maritime Authority Official Telegram Group