May 20, 2024

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2016(ኢዜአ)፦ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዲጂታል ስርዓትን በመተግበር ረገድ የተሻለ ስራ ማከናወኑን የፌደራል መንግስት የድጋፍና የሱፐርቪዥን ቡድን ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚመራና ከፌዴራል ተቋማት የተወጣጣ የሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ ወደስራ መግባቱ ይታወቃል።

ቡድኑም ከፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) የስራ ስምሪት በመቀበል በተመረጡና ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች የሚያደርገው የመስክ ምልከታ እስከ ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል።

በዚህም የፌደራል መንግስት የድጋፍና የሱፐርቪዥን ቡድን አባላት በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እንዲሁም በሞጆ ደረቅ ወደብ የስራ እንቅስቃሴን ተዘዋውሮ የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የፌደራል መንግስት የድጋፍና የሱፐርቪዥን ቡድን አስተባባሪና የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ፥ ኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ 98 ከመቶ በላይ ወጪና ገቢ ምርቶችን እንደሚያጓጉዝ ተናግረዋል፡፡

የድጋፍና የሱፐርቪዥን ቡድኑ በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤትና በሞጆ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ያደረገው ምልከታም ተስፋ ሰጪ የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ማረጋገጡን ገልጸዋል።

የሞጆ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ከ18 ሺህ በላይ ኮንቴነሮችን በማስተናገድ በ59 ሄክታር መሬት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የገቢና ወጪ ዕቃዎችን ደህንነት ለመጠበቅ በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤትና በሞጆ ደረቅ ወደብ ተርሚናል የተገጠሙ የደህንነት ካሜራና ዘመናዊ የዲጂታል አገልግሎት መልካም ጅምር መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ለማሻሻል የወሰዳቸውን የለውጥ እርምጃዎች የበለጠ ለማጠናከር በትጋት መስራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ተቋሙ በድጋፍና ሱፐርቪዥን ቡድኑ በጥንካሬና በውስንነት የተሰጡ ግብዓቶች በመጠቀም ለበለጠ ስኬት መስራት እንደሚኖርበትም አንተስተዋል።

የተመዘገቡ ስኬቶችን በተሞክሮነት ሌሎች ተቋማት እንዲማሩባቸውና መሻሻል ያለባቸው እንዲሻሻሉ ክትትል እንደሚያደርግም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያን የሎጀስቲክስ ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች እንዲጠናከሩ የሱፐርቪዥን ቡድኑ በቅርበት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተቋሙ የመንግስትን ውሳኔ ሚፈልጉ ጉዳዮች ከፖሊሲና ህግጋት ማሻሻያ ጋር የሚስተዋሉ ውስንነቶችንም ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ መፍትሔ እንዲያገኙ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)፥ በአፍሪካ ቀዳሚ የሎጀስቲክ መዳረሻ ለመሆን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በ5 ዓመቱ ዕቅድ ላይ ሞጆን ጨምሮ የሎጀስቲክስ መዳረሻ ወደቦችን አቅም በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ፣ ስመጥርና ብቃት ያለው ድርጅት ለመፍጠር ራዕይ ተሰንቆ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት እየተደረገ የሚገኘውን የማይተካ ሚና ለማስቀጠል በድጋፍና ሱፐርቪዥን ቡድኑ የተሰጡ ምክረ ሃሳቦችን በመውሰድ ለተሻለ ስኬት በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምሕረተዓብ ተክሉ፥ በድጋፍና ሱፐርቪዥን ቡድኑ ተቋማዊ የሎጀስቲክስ አልግሎትን ለማሳለጥ የተወሰዱ የአሰራር ማሻሻያዎችን በጥንካሬ መውሰዱን አንስተዋል፡፡

የመንግስትን ውሳኔ ከሚጠይቁ፣ ከፖሊሲና የህግ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ በውስንነት የተነሱ ተግባራት በዕቅድ ተይዞው እየተሰራባቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዘመናዊ የቴክኖሎጂ በመታገዝ የሎጀስቲክስ ተገልጋዮች ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የጉምሩክ ቅንጅታዊ አሰራርን የበለጠ እንዲሻሻል የተሰጡ ምክረ ሃሳቦች ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በመስክ ምልከታው በተቋሙ የተመዘገቡ ስኬታማ ተግባራትን ማስቀጠል የሚያስችሉና በውስንነት የታዩ ተግባራት ላይ የማሻሻያ ርምጃ እንዲወሰድ የቀጣይ አቅጣጫ ግብረ መልስ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ “ለጥረትዎ እሴት እንጨምራለን” በሚል መሪ ሃሳብ ተቋማዊ አቅም በማጎልበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሺፒንግና የሎጅስቲክስ አገልግሎት የመስጠት ተልዕኮን በማንገብ ወጪና ገቢ ምርቶችን በባሕርና የብስ እያጓጓዘ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነው።

ምንጭ፡ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢ.ዜ.አ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *