ቋሚ ኮሚቴው በማዕከሉ ውስጥ ለሰልጣኞች አገልግሎት የሚሰጡትን የመጀመሪያ እርዳታ ህክምና፣ ቤተ መፅሐፍት፣ የደህንነት መጠበቂያና የኮምፒውተር ማሰልጠኛ ክፍሎችን ተመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) በምልከታው ማዕከሉን ለመደገፍ የሚያስችል በቂ ግብዓት እንዳገኙ አብራርተው፣ ማሰልጠኛ ተቋሙ የእሳት አደጋና በባህር ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል መረዳት ተችሏል ብለዋል።
አካዳሚው የሚሰራቸው ሥራዎች ለሀገር ትልቅ አስተዋጾ ስላላቸው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የበለጠ አጠናክሮ መስራት እንደሚገባና ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የተከበሩ ዶ/ር እሸቱ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍራኦል ጣፋ የሎጅስቲክስ ትራንፎርሜሽኑ ባለፉት ዓመታት የተሻሉ ለውጦችን እንዳመጣ አብራርተው፣ ዘርፉን ማዘመን የህልውና በመሆኑ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሚፈለገው መልኩ እንዲጓዝ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።
የብሉ ኢኮኖሚን ለማሳደግ እና የባህር ላይ ሥራ ለቱሪዝሙ ፍሰት ከፍተኛ ሚና ስላለው በባህር ላይ የሚሰራን የሰው ሀይል ተወዳዳሪ እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ፍራኦል ጠቁመዋል።
የብሉ ኢኮኖሚ ፅንስ ሐሳብ የተጀመረው ቅርብ ጊዜ በመሆኑ በቀጣይ አገራችን በዘርፉ ተጠቃሚና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
አካዳሚው ባለፉት 9 ወራት በማሪታይም 552 በሎጂስቲክስ ደግሞ 660 ሰልጣኞችን በማብቃት የባህረኝነት መሰረታዊና መኮነንነት ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎች በአብዛኛው በመካከለኛው ምስራቅ ባሉ መርከቦች ተቀጥረው እንደሚሰሩና የሎጂስቲከስ ሰልጣኞች ደግሞ በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በማገልገል ላይ እንደሚገኙ የአካዳሚው ዲን ቺፍ ቴዎድሮስ ሚሊዮን አስታውቀዋል።
በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው በባህር ላይ ህይወቱን መስዋዕት አድርጎ የሰውን ህይወት ማዳን የሚያስችል ስልጠና እንደሚሰጥ በአካል እንዳየ በመግለጽ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የኢትዮጵያ መርከበኞች እያገለገሉ በመሆናቸው ለሀገራችን ትልቅ ስኬትና ብሔራዊ ኩራታችንን ከፍ የሚያደርግ ነው ሲል አድናቆቱን ገልጿል።
ምንጭ፡ ኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ፌስቡክ ገጽ