Ethiopian Maritime Authority

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን

መንግሥት የሎጂስቲክስ ዘርፉን በማዘመን የገቢና የወጪ ንግድን ቀልጣፋ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው::

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ ዘርፍ በማዘመን የገቢና የወጪ ንግድን ቀልጣፋ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎች እና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ባለው የፊያታ (FIATA) ዲፕሎማ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች አስመርቋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት መንግሥት ለዘርፉ ሪፎርም ልዩ ትኩረት በመስጠት ስትራቴጂ ቀርጾ እየሰራ ይገኛል።

ሎጂስቲክስ ዕቃዎችን ማጓጓዝ ብቻ ሳይሆን የሀገር ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር የሚያገናኝ መረብ ነው ብለዋል።

መንግሥት የወጪና የገቢ ምርቶችን በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት ለማሳለጥ የሎጂስቲክስ ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ኃይል ለማጠናከርና ለማዘመን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በዲጂታል ኢኮኖሚ የተጀመሩ የብልጽግና ጉዞዎች ውጤታማ መሆን የሚችሉት አስተማማኝ የሎጂስቲክስ ሥርዓት ሲኖር ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሎጂስቲክስ ዘርፍ ካልዘመነ በስተቀር ምርቶችን በጥራት፣ በሰዓቱና በቅናሽ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ እንደማይቻልና የሀገር ውስጥ ምርቶችም በዓለም መድረክ ተወዳዳሪ መሆን እንደማይችሉ አስረድተዋል።

ዛሬ የተመረቁት የፊያታ ዲፕሎማ ባለሙያዎች የሀገሪቱን የአቅርቦት ሰንሰለት በማዘመን በኩል ትልቅ አደራና ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ሰልጣኞችና የዘርፉ ተዋናዮች ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ በሚመጡበት ወቅት የሚፈጠሩትን ዕድሎች ለመጠቀም ከአሁኑ ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍራኦል ጣፋ በበኩላቸው በሀገሪቱ የሎጂስቲክስ ሥርዓትን ማዘመንና ወቅቱን የዋጀ አሠራር መዘርጋት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ አጠቃላይ የዘርፉን ትራንስፎርሜሽን ማሳለጥ የሚያስችል የአሥር ዓመት ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተግዳሮቶችና የኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ ለመቋቋም የራስን ሥርዓት በራስ አቅም መገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የውጭ ኢንቨስትመንት ዕድልን በአግባቡ ለመጠቀምና የሀገሪቱን የንግድ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ በሳይንሳዊና በዘመናዊ ዕውቀት የሰለጠኑ ባለሙያዎች ሚና የማይተካ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎች እና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዳዊት ውብሸት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ይህ የፊያታ ዓለም አቀፍ ሥልጠና በኢትዮጵያ ያለውን የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ትልቅ እምርታ መሆኑን ገልጸዋል።

ማኅበሩ አቅምን በመገንባትና የገበያ ትስስርን በመፍጠር በኩል ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ሰልጠኞች በበኩላቸው የወሰዱት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና የሙያ ብቃታቸውን ከማሳደግ ባለፈ ሀገራቸውን በላቀ ደረጃ ለማገልገል ትልቅ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በስልጠናው የተሳተፉት አምባዬ ገብርኤል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና መውሰዳቸው የስራ ብቃታቸውን ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ አለው ብለዋል።

የተሻለ ሥራ ለመሥራትና ሀገራቸውን በላቀ ሁኔታ ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

ከፔቭ ሎጂስቲክስ የመጡትና የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት ይርጋለም አዲስ በበኩላቸው፣ ስልጠናው ትልቅ እውቀትና ክህሎት እንዳስጨበጣቸው ገልጸዋል።

#Ethiopian_News_Agency#ኢዜአ#ENA

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *