Ethiopian Maritime Authority

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን

ባለስልጣኑ የሎጀስቲክ አገልግሎትን በማሳለጥ አበረታች ተግባር እያከናወነ ይገኛል — ቋሚ ኮሚቴው

ሚያዝያ 21፣ 2018 ዓ.ም፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣንን የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።
የከተማ፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሰቢ የተከበሩ መሀመድ አብዶ (ፕ/ር) ባለስልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የማሪታይም ሎጀስቲክ አገልግሎትን በማሳለጥ፣ በመከታተልና በመቆጣጠር ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ የሞጆ ደረቅ ወደብ በርካታ ጭነቶችን እንዲያስተናግድ ዘመናዊና ዲጅታላይዝ በሆነ መልኩ መገንባቱ አበረታች መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አመላክተዋል።

በተያያዘም የዘርፉን አገልግሎት ለማሳለጥ እንዲሁም ሕገ-ወጥ ደላሎችን ለመቀነስ ባለስልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የመልቲ ሞዳል እና ሚኒ ሞዳል የጭነት አገልግሎት ሽፋን ከማስፋፋት አኳያ ለአምስት የግል እና የመንግሥት ተቋማት ፈቃድ መስጠቱ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በሌላ መልኩ መርከቦች በሚፈለገው መልኩ ጭነቶችን ለማስተላለፍ ዓለም ዓቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታው ተፅዕኖ መፍጠሩ በእጥረት እንደተገመገመ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ መሀመድ አብዶ (ፕ/ር) ገልፀዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ም/ሰብሳቢ የተከበሩ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) ዘርፉ እንደ ሀገር ትኩረት ተሰጥቶት የተሻለ አፈጻጸም ያሳየ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ የገቢና ወጪ አማራጭን ከማስፋት አንፃር በጥናት ላይ ተመስርቶ ዲፕሎማሲን በማስፋት እየሰራ መሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ምክትል ሰብሳቢው አክለውም ባለስልጣኑ አገልግሎቱን ፈጣንና ቀልጣፍ ለማድረግ ከአጋር አካላት እና ከሌሎች አቻ ሀገራት ልምድ በመውሰድ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍራኦል ጣፋ በበኩላቸው የመልቲ ሞዳል ሽፋንን ለማስፋት በሎጂስቲክ ዘርፍ የግሉን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፤ የባህር ደህንነትና አደጋን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ሕጉን መሠረት በማድረግ ከባህር ማህበራት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለስልጣኑ አጠቃላይ የገቢና ወጭ አገልግሎቱን ለማሳለጥ ከሎጀስቲክስ እና ትራንስፖርት ሚኒስቴር ተግባራት ጋር በማስተሳሰር ስርዓቱን ዲጅታላይዝ በማድረግ ደላላን በመከላከል የዋጋ ጭማሪን ለመቀነስ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ሲል ዜና ፓርላማ ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *