በሎጂስቲክስ ዘርፉ ለሚሰማሩ 100 ያህል ወጣት ሴቶች ያለ ምንም ክፍያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጠና መሰጠት መጀመሩን፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የሎጂስቲክስ ትራስፎርሜሽን ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ ለማ ለሪፖርተር እንዳሉት፣ ሥልጠናውን ያለ ምንም ክፍያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየወሰዱ ያሉት ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ወጣት ሴት ተማሪዎች ናቸው።

የጋራ ተጠቃሚነትን ባገናዘበ መንገድ በቀመር ተሠልቶ የሁሉም ክልሎች ሠልጣኞች ተሳታፊ መደረጋቸውን የጠቀሱት አቶ ወርቁ፣ ሥልጠናው በሎጂስቲክስ ዘርፍ ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠርና የሴቶች ተሳትፎን ማሳደግ ላይ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሠልጣኞቹ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ላለው ዲፕሎማ ከዘጠኝ ወራት እስከ አንድ ዓመት ሠልጥነው በሎጂስቲክስ ዘርፉ ውስጥ እንዲሰማሩ በማድረግ፣ ለዘርፉ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። 

የታሰበው ለውጥ እንዲመጣ ሠልጣኞች ሥልጠናቸውን ሲጨርሱ ወደ ዘርፉ በቀጥታ እንዲገቡ ለማድረግ፣ ባለሥልጣኑ የሥራ ዕድል በማመቻቸት ረገድ ሚናው ምን ይሆናል ተብለው የተጠየቁት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ስላለ እናግዛቸዋለን ቁርጠኝነት ነው ያለው፤›› ብለዋል።

ሠልጣኞቹ ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ሲደረግ የቀሰሙትን ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ፈተና እንደሚወስዱ ያመላከቱት አቶ ወርቁ፣ ፈተናውን የሚያልፉትን ከኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር፣ እንዲሁም በዘርፉ ላይ ከሚሠሩ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ዕቅድ መያዙን አስረድተዋል።

በዘርፉ ያለውን የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍና የባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ስምምነት ተደርሶ እየተሠራ መሆኑን አቶ ወርቁ አክለዋል።

ሥልጠናው ከዓለም ባንክና ከመንግሥት በተገኘ ድጋፍ፣ በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣንና በኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር አማካይነት እየተሰጠ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

የሥልጠናው ቀጣይነት ምን እንደሚመስል የተጠየቁት አቶ ወርቁ፣ ‹‹በሚገኝ በጀት ላይ የተመሠረተ ነው፤›› ብለዋል።

Source: Reporter ሃይማኖት ደስታ

ቀን: May 28, 2025

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *