ከየካቲት 16-28 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ሲካሄድ የቆየው 4ኛው ዙር የፊያታ ዲፕሎማ የአሠልጣኞች ሥልጠና ፕሮግራም ማክሰኞ የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በተከናወነ ደማቅ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡
በዕለቱም የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ የኋላእሸት ጀመረ (ኢንጅ.)፣ የኢትዮጵያ ፍሬት ፎርዋርደርስ ኤንድ ሺፒንግ ኤጀንትስ ሊቀመንበር ወ/ሮ ኤልሣቤጥ ጌታሁን፣ የኢትዮጵያ ፍሬት ፎርዋርደርስ ኤንድ ሺፒንግ ኤጀንትስ ምክትል ሊቀመንበርና የዓለምአቀፉ የዕቃ አስተላላፊዎች ማኅበራት ፌዴሬሽን (ፊያታ) የአየር ጭነት ተቋም ሊቀመንበር፣ አቶ ዳዊት ውብሸት፣ የፊያታ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚደንትና የፊያታ ዲፕሎማ የአሠልጣኞች ዋና አሠልጣኝ፣ ሚስተር ቶማስ ሲም፣ በፊያታ የአፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ሊቀመንበር፣ አቶ ሳላሃዲን ከሊፋ፣ የትሬድማርክ አፍሪካ ሊሚትድ የኢትዮጵያ ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ አቶ አብነት በቀለ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎና ሎጂስቲከስ አገልግሎት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አቤል ዓለሙን ጨምሮ የማኅበሩ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ሠልጣኞች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የመገናኛ ብዙኃን ተገኝተው ነበር፡፡
የመግቢያ ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ኤልሣቤጥ በመልዕክታቸው ማኅበሩ የሚሰጠውን የሥልጠና ፕሮግራም በማስፋትና ለብዙኃን ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ የሥልጠና ማዕከል ለመገንባት የሚችልበትን ቦታ መንግሥት እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ከሊቀመንበሯ በመቀጠል መልዕክታቸውን ለታዳሚው ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር የኋላእሸት በማኅበሩ በኩል እየተደረጉ ላሉት ጠንካራ የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ዕውቅና በመስጠት ምሥጋናቸውን ቸረዋል፡፡
“እንደ የፊያታ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚደንትነቴ ይህን ጠቃሚ የሥልጠና ፕሮግራም በስኬት እንዲከናወን ላደረገው የኢትዮጵያ ፍሬት ፎርዋርደርስ ኤንድ ሺፒንግ ኤጀንትስ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቴን ማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡” በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት ዋና አሠልጣኝ ሚስተር ቶማስ ሲም ማኅበሩ የሥልጠና ፕሮግራሙን በአመርቂ ሁኔታ እንዲያጠናቅቅ ከዚህ ቀደም የነበሩት ስኬቶቹ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለዋል፡፡
የሥልጠናውን ሁኔታ የተመለከቱ አስተያየቶች ከተለያዩ ሠልጣኞች የቀረቡ ሲሆን አሠልጣኙ ዓለም አቀፉን የአሠራር ሥርዓት ሠልጣኞች በአግባቡ እንዲረዱ ማድረጋቸው ሠልጣኞች ያላቸውን ዕውቀት በተገቢው መልኩ ለማስተላለፍ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡ የአሠልጣኙ የካበተ ዕውቀት እና የአቀራረብ መንገድ የተጨናነቀ የሚመስለውንና ብዙ ጥረት የሚያስፈልገውን የሥልጠና ወቅት ሳይሰላቹ እንዲያሳልፉት እንደረዳቸው በመግለጽ ምሥጋናቸውን የማስታወሻ ስጦታ ለአሠልጣኙ በማበርከት ገልጸዋል፡፡
አሠልጣኙ የማስታወሻ ስጦታ የተበረከተላቸው ከሠልጣኞች ብቻ አልነበረም፡፡ ፕሮግራሙን በታቀደለት ጊዜ፣ ደረጃውን በጠበቀ መልኩና በማይረሳ መንገድ በመስጠታቸው ማኅበሩ የዕውቅና ሠርቲፊኬትና ስጦታ አበርክቶላቸዋል፡፡
በሌላ መልኩ “ይህን ወቅታዊ የሆነ ሥልጠና በማዘጋጀት ያለንን ዕውቀት እንድናዳብርና ዓለም አቀፍ የሆኑ ተሞክሮዎችን እንድናገኝ ማኅበሩ ለተጫወተው ሚና ምሥጋናችን እናቀርባለን፡፡” በማለት የ4ኛው ዙር የአሠልጣኞች ሥልጠና ተሳታፊ ባለሙያዎች ለማኅበሩ ስጦታ አበርክተዋል፤ ስጦታውንም የማኅበሩ የሥራ አመራር ቦርድ አባላትና የጽ/ቤቱ ባልደረቦች በጋራ ተቀብለዋል፡፡
ሥልጠናውን በአግባቡ ወስደው ላጠናቀቁ ሠልጣኞች የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችላቸውና ከፊያታ በቀጥታ የሚላከውን የማረጋገጫ ሠነድ ከቅርብ ቀናት በኋላ የሚቀበሉ ይሆናል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ሥልጠናው እንዲሳካ ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉ ተቋማት የምሥጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡
ለፕሮግራሙ የመዝጊያ ንግግር በማድረግ እልባት የሰጡት በፊያታ የአፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ሊቀመንበር እና የማኅበሩ የሥልጠና ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሳላሃዲን ከሊፋ ናቸው፡፡ አቶ ሳላሃዲን የፊያታ ዲፕሎማ ሥልጠና ከዚህ በበለጠ መልኩ እንዲስፋፋ ይህንን የሥልጠና ፕሮግራም የሚሠጡ አሠልጣኞች ቁጥር መጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስምረውበታል፡፡
ማኅበሩ የፊያታ ዲፕሎማ የአሠልጣኞች ሥልጠና ፕሮግራምን ከዚህ በፊት እ.ኤ.አ በ2010፣ በ2017 እና በ2018 ለሦስት ጊዜያት ያህል ያካሄደ ሲሆን 4ኛው ዙር የፊያታ ዲፕሎማ የአሰልጣኞች ሥልጠና መርሐ-ግብር ከየካቲት 16-28 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡