አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ወቅታዊና እያደገ የመጣውን የሎጂስቲክስ አቅም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ÷ የባህር በር የአንድ ሀገር ጥቅል የምርት እድገትን ከ25 እስከ 30 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥናትን ጠቅሰው መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ አኳያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የወጭና ገቢ ንግዷን በጅቡቲ በኩል የምታከናውነው ኢትዮጵያም የባህር በር በማጣቷ ምክንያት በዓመት 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ለወደብ ኪራይ ታወጣለች፡፡
ይህንን አስመልክቶም የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ እንዳሉት÷ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ 9 ሁለገብ እና 2 ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ ለማሳለጥ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ይሁን እንጂ የባህር በር አለመኖሩ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ነው ያስረዱት፡፡
የባህር በር አለመኖር በተለይ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው እንደ ፍራፍሬ ያሉ ቶሎ የሚበላሹ ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቆ በፍጥነት ተደራሽ በማድርግ ረገድ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህም በተወዳዳሪነት ላይ የራሱን እክል በመፍጠር ወጪ ንግዱ እንዲቀንስ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወደብ ባለመኖሩ ምክንያት እቃዎች በሚገቡና በሚወጡበት ወቅት በወደብ የሚኖራቸው ቆይታ ከፍተኛ ወጭ እንዳለውና ይህም የዋጋ ንረት እንዲከሰት እንደሚያደርግም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሎጅስቲክ ወጭን በማቃለል የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ወሳኝ ሚና አለውም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ካላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ አንጻር የባህር በር መኖሩ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለውም አንስተዋል፡፡
ይህም የሎጂስቲክስ ዘርፍ ከማሳለጥ ባሻገር ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ለስራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት፡፡
የዜና ምንጭ፡ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ድህረ-ገጽ