March 27, 2024

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት መሳተፍ ለሚፈልጉ ድርጅቶች እንዲመዘገቡ ህዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ባወጣው ማስታወቂያ ጥሪ ማስተላለፉን ተከትሎ ወደ ዘርፉ ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉ በሎጅስቲክስ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ታህሳስ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በባለሥልጣን መስሪያቤቱ በተጠራ የውይይት መድረክ የምዝገባ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ጠይቀዋል፡፡በስብሰባው ላይ የተሳተፉት በሎጅስቲክስ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ባለቤቶችና ተወካዮች ለመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት አከናዋኝነት የተቀመጠውን መስፈርት ለማሟላትና ለመመዝገብ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልፀው፤ ነገር ግን ከመስፈርቶቹ መካከል መሬት የማገኘት ሂደቱ ረጅም በመሆኑ እንዲሁም በቂ ዝግጅት በማድረግ ወደ ዘርፉ በመግባት የሎጅስቲክስ አገልግሎት በማሳለጥ ረገድ የግሉ ዘርፍ ለሀገር እድገት የድርሻውን መወጣት እንዲችል ባለሥልጣን መ/ቤቱ የምዝገባውን ጊዜ ሊያራዝምልን ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡


ውይይቱን የመሩት በባለሥልጣን መስሪያቤቱ የሎጅስቲክስ አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ያለው ተስፋዬ በበኩላቸው በሎጅስቲክስ ስትራቴጅ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጎልበት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርትን ቀስ በቀስ ለውድድር ክፍት ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቆ ማስታወቂያ መውጣቱን አስታውሰው፤ ሆኖም ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠን በሚል በስልክ፣ በደብዳቤና በአካል ጥያቄዎች እየቀረቡ በመሆኑ የዘርፉን ድርጅቶችና ኩባንያዎች ማወያየትና መፍትሔ ለማስቀመጥ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ኃላፊው አያይዘውም በውይይቱ ላይ ጠቃሚ ግብዓት መገኘቱን፣ የግሉ ዘርፍ በመልቲ ሞዳል ኦፕሬተርነት ለመሳተፍ ያሳያችሁት ዝግጅት የሚያበረታታ በመሆኑ፣ እያደገ የመጣውን የሀገሪቷን የገቢ ንግዱን ለማሳለጥ የበኩላችሁን ድርሻ ለመወጣት ያሳያችሁት ፍላጎት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፣ የቀረቡ ጥያቄዎች እና ከውይይቱ የተነሱትን ግብዓቶች ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው የሰነድ ማቅረቢያ ቀናት ማራዘም እንደሚገባ በተቋሙ የበላይ አመራሮች የታመነበት በመሆኑ ለስንት ጊዜ እንደሚራዘም በቀጣይ በማስታወቂያ እንደሚገለጽ አብራርተው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *