
የኢትዮጵያን መርከቦች ከመጠቀም አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሄደ
ሰኔ 18/2017 ዓ.ም :- የኢትዮጵያን መርከቦች ከመጠቀም አንፃር የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመቅረፍ እቃዎቻቸውን በቋሚነት በመርከብ ከሚያስጭኑ(ዌቨር) አካላት ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

መድረኩን የመሩት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ የመድረኩ ዓላማ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ እና ብሔራዊ ኩራት መሆኑን በመጠቆም የሴክተሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ በመነጋገር የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን ተናግረዋል ።
በሂደቱም በሎጂስቲክስ የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅን እና ዘርፋን ተወዳዳሪ ማድረግን አጣጥሞ ማስኬድ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም በሴክተሩ የሚሰጡ አገልግሎቶች ቅልጥፍና እና የሎጂስቲክስ አፈፃፀም ለመጨመር እንዲሁም ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የትራንስፖርት ዋጋን ለማሻሻል በርካታ ስራዎችን እየሰራን ነው ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የተናገሩ ሲሆን ከዋጋ ተወዳዳሪነት፣ ከቅልጥፍና፣ ከስኬጁል እና ከወደብ መዳረሻ ውስንነት ላይ ያሉ ጉዳዮች መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ከቤቱ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ክቡር ዶ/ር በሪሶ አመሎ ሲሆኑ ከቀይ ባህር ወቅታዊ ችግር የተነሳ የሌሎች ሀገራት መርከቦች መሥመር በመቀየራቸው የኢትዮጵያን ካርጎ በብቸኝነት እያጓጓዘ ያለው ድርጅታችን ነው ብለዋል።
የመርከቦች ቁጥር ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን በመጠቆም ከመዳራሻ እጥረት ጋር ተያይዘው ያሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ቅልጥፍን ለመጨመር እና አገልግሎቶችን ለማዘመን አሰራሮችን ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ ጊዜን የሚያባክኑ አሰራሮች እንዲሻሻሉ፣ ተወዳዳሪነት ላይ ተፅእኖ እንዳይፈጠር የተጋነነ የትራንስፖርት ዋጋ ካለ እንዲስተካከል አቅጣጫ የሰጡ ሲሆን የሴክተሩን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በተቀናጀ አግባብ መሠራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ ክቡር ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር በሪሶ አመሎ እና የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የስራ ሀላፊዎች እና የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
Source: Ministry of Transport & Logestics