March 22, 2024
ሚያዝያ 9 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ፡ የትንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ትሬድ ማርክ አፍሪካ ከተባለ ድርጅት ጋር የጭነት ትንስፖርት አገልግሎትን ለማሳለጥ የሚያሥችል የተሽከርካሪ አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት ለማልማት የፕሮጀክት ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡

የስምምነት ሰነዱን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ እና የትሬድ ማርክ አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ እውነቱ ታየ የተፈራረሙ ሲሆን ክቡራን ሚኒስቴር ዴኤታዎች አቶ ደንጌ ቦሩ እና ኦቶ በርኦ ሀሰንም በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የሀገራችንን የጭነት ትራንስፖርት በማዘመን ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን ማድረግ፣ አገልግሎቱን ለዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብና ፍጥነትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ብለዋል፡፡

ይህንንም በሚገባ ለማሳካት የተቀናጀ የተሽከርካሪ አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት መዘርጋት አስፈልጓል ያሉ ሲሆን ፕሮጀክቱ የጭነት እንቅስቃሴን በማቀናጀትና በማዘመን የአንድ ማዕከል ቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት የሚያሥችል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ስምምነት የተደረገበት የተቀናጀ የተሽከርካሪ አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት በሚፈለገው ሁኔታ እንዲፈፀምና የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስገኝ በጋራ ሁላችንም ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ያሉ ሲሆን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለፕሮጀክቱ እውን መሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ክቡር ሚኒስትሩ ዶ/ር አለሙ ስሜ አረጋግጠዋል፡፡

ትሬድ ማርክ አፍሪካ የንግድ ወጪን በመቀነስና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎትን በማሳለጥ የሀገራትን የልማትና የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ ስራዎችን የሚሰራ ድርጅት እንደሆነ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ እውነቱ ታየ ገልጸዋል፡፡

ትሬድ ማርክ አፍሪካ የገንዘብና የሙያ ድጋፍ በማድረግ ፕሮጀክቱን የሚያለማ ሲሆን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ደግሞ ፕሮጀክቱን በበላይነት በመምራት የሚያስተባብርና ሲጠናቀቅም የሚያስተዳድር ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *