ሐምሌ 23፣2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ፅ/ቤት በዓለም ባንክ የገንዘብ እና ሙያዊ ድጋፍ አማካኝነት የኢትዮጵያን ሎጅስቲክስ አፈፃፀም ሪፖርት ለ3ኛ ጊዜ በራስ አቅም በሀገር ውስጥ ገለልተኛ የጥናት ቡድን አሰርቷል፡፡ በጥናት ሪፓርቱ ላይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በራዲሰን ብሉ ሆቴል ምክክር አድርጓል።
በምክክር መድረኩ የ2023 የኢትዮጵያ የሎጅስቲክ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የጥናት ቡድኑ አባል እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ም/ኘሬዝዳንት ዶ/ር ማቲዮስ ኢንሰርሙ እንደገለፁት እ.ኤ.አ በ2023 የኢትዮጵያ የሎጅስቲክ አፈፃፀም ቀደም ሲል የዓለም ባንክ ሲጠቀምባቸው በነበሩ መለኪያዎች መሰረት የተለካ ሲሆን ከባለፉት 2020 እና 2021 ከነበረው አፈጻጸም መሻሻል አሳይቷል፡፡ በዚህም መሰረት ጠቅላላ ውጤቱ ከተቀመጠው 5 ነጥብ ውስጥ 2.94 ላይ እንደደረሰ እና ይህም በ2021 ከነበረው 2.55 አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ15 በመቶ ብልጫ እንዳለው የሚያሳይ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
በጥናት ሂደቱ ከ303 በላይ በግልና በመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳትፉ መሆኑም የተወሳ ሲሆን በግንዛቤ ዳሰሳ ሪፖርቱ (perception survey report) ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለጹት በመለኪያዎች መሰረት ዝቅተኛ አፈጻጸም የተመዘገበባቸው ዘርፎች ተለይተው የማሻሻያ ስራ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍራኦል ጣፍ በዚህ ጥናት ላይ የተሳተፉትን አካላት አመስግነው ሀገራት በውስጥ አቅም የራሳቸውን የሎጅስቲክስ አፈፃፀም መለካታቸው በዘርፉ ያሉ ዕድሎችን እና ተግዳሮቶችን በመለየት ለመስራት እንደሚያግዝ እና ባለሥልጣኑ እንደ ተቋም የዘርፉ ተዋናዮችን አቀናጅቶ በመስራት ለቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማምጣት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
Source: Ethiopian Maritime Authority Official Telegram Page