የመልቲሞዳል ትራንስፖርት አከናዋኝ የንግድ ሥራ ፈቃድ ለመስጠት እና ብቃትን ለማረጋገጥ የተዘጋጀ ረቂቅ መመሪያ ላይ የጽሁፍ አስተያየት ለመሰብሰብ የወጣ ማስታወቂያ
የመልቲሞዳል ትራንስፖርት ዘርፉን ቀስ በቀስ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ክፍት ለማድረግ በሎጅስቲክ ፖሊሲ ላይ የሰፈረውን ድንጋጌ ስራ ላይ የማዋል ሂደት ተጀምሯል፡፡ በዚህም መሰረት በንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980 አንቀጽ 21 (4) (በ) እና በማሪታይም ዘርፍ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 549/1999 አንቀጽ 18 (ለ) ላይ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ለመልቲሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት አከናዋኝ የንግድ ሥራ ፍቃድ ለመስጠት እና ብቃትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ አዘጋጅቷል፤
ረቂቅ መመሪያው የሚከተሉትን ዋና ዋና ጉዳዩች አካቷል፡፡ እነርሱም ፡-
– የመልቲሞዳል ትራንስፖርት ሥራ ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል መስፈርት
– የመልቲሞዳል ትራንስፖርት አከናዋኝ ተግባራት
– የመልቲሞዳል ትራንስፖርት አከናዋኝ ግዴታዎች
– ስለ ሥራ ፈቃድ ዕድሳት፤ ዕገዳና ስረዛ ናቸው
ማንኛውም ሰው በመመሪያው ላይ ያለውን አስተያየት ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ዕለት ጀምሮ ባሉት 15 ተከታታይ የስራ ቀናት ውስጥ አስተያየቱን በጽሁፍ ለማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን (ሜክሲኮ ዲአፍሪክ ሆቴል ፊት ለፊት፤ ታደሰ ተፈራ ህንጻ፤ 6ኛ ፎቅ፤ ቢሮ ቁጥር 6-3) ማቅረብ ወይም በኢሜል አድራሻ (logistics.transformation.office@gmail.com) እንዲልክ እንጠይቃለን፡፡ የረቂቅ መመሪያው ቅጅ ከማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን ድህረ-ገጽ (https://etmaritime.com) ማግኘት ይችላል::
ማንኛውም ሰው የረቂቅ መመሪያውን በተመለከተ የተደራጀውን መዝገብ መመልከት ወይም አስፈላጊውን ወጪ ሸፍኖ ቅጂውን መውሰድ ይችላል፡፡

በኢፌዲሪ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን